አርበኛ-ፋኖ| ኢትዮጵያኖች አረቢያ ስደት ሞት መግለጫ EPPF Communique statement on Ethiopians Abused in Arabia
የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር (ኢህአግ) No. 2020/03 Sep 4, 2020
በመካከለኛው ምስራቅ ሳውዲ አረቢያና የመን በስደት ላይ በሚገኙ ዜጎቻችን ሕይወት ላይ እየደረሰ ያለው ችግር እና የመንግስት ቸልተኝነትን አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ በሀገራችን ካለው ነባራዊ የኢኮኖሚና የፖለቲካ አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ዜጎቻችን በስደት ወደ ተለያዩ የአለም ሀገራት በመጓዝ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ሕይወታቸውን እየመሩ ይገኛሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በመካከለኛው ምሥራቅ ፣ ሳውዲ አረቢያና የመን በስደት ላይ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ተደራራቢ ችግሮች እየደረሰባቸው እንደሆነ ይታወቃል፣ በጉዳዩ ላይ ግን መንግስት በትኩረት እየሰራ እንዳልሆነም ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል፡፡ መንግስት የነዚህ ስደተኞችን ስቃይ በቀጣይ ለሚመጡ ለሌሎች ስደተኞች መቀጣጫ እንዲሆንም ለማድረግም ይሆናል የሚል ግምትን ያጭራል፡፡ የአንድ ሀገር መንግስት ዜጎቹን በስደትም ይሁን በሀገር ውስጥ ደህንነታቸውን ማስጠበቅ እና ሰብአዊ መብታቸው ማሰከበር ይጠቅበታል፡፡ በዋናነትም ህገወጥ ዝውውሮችን መግታትና መቆጣጠር የሚያስችሉ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ማድረግ ተቀዳሚ ተግባርም የመንግስት ሊሆንም ይገባል፡፡ ይኽንን ሀላፊነቱን መወጣት ባለመቻሉ ዜጎች እንደ ሳውዲና የመን በመሳሰሉ ሀገራት ውስጥ ከፍተኛ ለሆኑ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተዳርገዋል፡፡ ይልቁንም እየደረሰባቸው ያለውን በደል ለሰብአዊ መብት ተቋማት እና በማህበራዊ ሚዲያ እንዳያጋሩ፣ የድረሱልን ጥሪ እንዳያደርጉ ማስፈራሪያ እንደሚደረግባቸውም በመገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡
በሥልጣን ላይ ያለው መንግስት ለዜጎቹ ምቹ የሆነ ከባቢ እና የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ከመስራት ይልቅ የዘውግ ሥርዓቱን ለማስከበር የሚያደርገው ጥረት ከፍተኛ በመሆኑ በሀገር ውስጥ የተረጋጋ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ኑሮ መሰናክል ሆኖ ቆይቷል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ 5.5 /አምስት ነጥብ አምስት/ ሚሊዮን ዜጎች በረሀብ አለንጋ እየተገረፉ እንደሚገኙ የተባባሩት መንግስታት ዘገባ ያመላክታል፡፡ ሀገራችን ከገባችባቸው እጅግ ብዙ ፈተናዎች ውስጥ ለመውጣት የአብይ መንግስት የብሔር ፖለቲካን መሰረት ያደረገውን ሕገመንግስታዊ ሥርዓት ለመቀየር ፍላጎት ባለማሳየቱ ዘላቂ መፍትሄ እንዳይገኝ ምክንያት ሆኗል፡፡ ከዚህ በኋላም መንግስት በዲሞከራሲያዊ መንገድ ሥልጣኑን በህዝብ ለተመረጠ አካል ለማስረከብ ዝግጁ አለመሆኑን ማሳያ ተደርጎ በሚወሰደው ድርጊቱ የተለያዩ የፖለቲካ አመራሮችን በሀሰት በመወንጀል ከፖለቲካው ሜዳ ገለል ለማድረግ አበክሮ እየሰራ እንደሆንም እንገነዘባለን፡፡ በዚህም ምክንያት አሁን ላለንበት የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ውጥንቅጥ ተዳርገናል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንድትቀጥል መንግስት ሥልጣኑን መልቀቅ እና ለህዝብ ማስረከብ ይኖርበታል፡፡ ይህ ሊሆን ካልቻለ ግን የመንግስት ኃይል በተለያየ አቅጣጫዎች አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ እንደሚጥል ከወዲሁ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አርበኞች ግንባር መንግስት በሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጪ በዜጎቻችን ላይ የሚፈፀመውን የመብት ጥሰት በፅኑ ያወግዛል፡፡ ግንባሩ ከሚታገልባቸው ዋነኛ አላማዎች መካከል የዜጎችን ሰብአዊ መብት ማክበርና ማስከበር፣ በኢኮኖሚ እኩል የመጠቀም መብት፣ በኢትዮጵያዊነታችን በሀገር ውስጥም ይሁን ከሀገር ውጪም የህግ ከለላና ጥበቃ የማግኘት እና ሰብአዊ መብቶቻችንን የማስከበር ግዴታ የመንግስት ድረሻ እንደሆነ ያምናል፡፡ ይሁንና የአብይ መንግስት በወገኖቻችን ላይ ለሚደርሰው በደል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ አለመሆኑን ይገነዘባል፡፡ ስለሆነም መንግስት በስደት ላይ የሚገኙ ወገኖቻችንን ለመመለስ እንዲንቀሳቀስ እና እስከሚመለሱ ድረስም አለማቀፍ የሰብአዊ መብቶችን መሰረት ያደረገ የመንግስትነት ተግባሩን በመወጣት ወደ ሀገራቸው እንዲመልሳቸው ጥሪ እናደርጋለን፡፡ አንድነት ሀይል ነው! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !!! ምንጭ፡ Human Rights Watch